App logo

Abel Abuna

@abelabuna

108

friends

ኢየሱስ ማስተካከያ የሌለው ትክክለኝነቴ ነው!! በምህረትህ አትቅጣኝ አንድ አጭር ገጠመኜን ላውጋቹ በአቤል አቡና ስራ እንዳለው ሰው በጠዋት እወጣለው፤ የምወጣው በጠዋት ከማጨሳት አንድ ኒያላ ጀምሮ ማታ አቅሌን እስከሚያስተኝ የአበሻ አረቄ (ቀሻ) ለመጠጣት ነው እንጂ እዚህ ግባ የሚባል የህይወት ግብ ይዤ የወጣሁበት ቀን ትዝ አይለኝም። ከሁሉ ነገር ራሴን ስላራኩት አለሜን ሱሴ ህልሜን ሱስ ዕቅዴን ሱስ አድርጌ ከእግዚአብሔር መንገድ፣ከራሴና ከህልሜ ርቄ እኖር ነበር። ያን ጊዜ ምን ትፈልጋለህ ቢሉኝ ጭስ ለምን ትሄዳለህ ቢሉኝ ለጭስ ነበር መልሴ። ካላጨሽኩ ቁርስ ስለማይበላልኝ ብዙ ጊዜ ቁርሴን ሳልበላ ከቤቴ እወጣ ነበር። በቀን አንዴ እበላ ስለነበር ሰውነቴ መልኬ ሁሉ ነገሬ የተበላሸና ውበት አልባ ነው። እኔ ለሱሴ የነበረኝ ፍቅር በዙሪያዬ የማውቃቸው ሰዎች ለፍቅረኛቸውና ለትዳር አጋራቸው አልነበራቸውም ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ሀሉንም ነገሬን ሰጥቼው እኖር ነበር፤ ጊዜዬን ገንዘቤን ሀሳቤንና አቅሜን ሁሉ አስገዝቼለት ነበር። ያልሸጥኩለት ጫማ ልብስና መፅሐፍ የለም መፅሐፍ ቅዱሴን ጨምሮ። ጠዋት በሰላም እወጣለው ማታ ድምፄን አጥፍቼ በአጥር ዘልዬ እገባለው። በነጋታው የትናቱን ኑሮ ዛሬ ደግማለው። አንድ ቀን ጠዋት ግን ከቤት ልወጣ ስል እናቴ "አቤልዬ" ብላ ጠራችኝ በሱሴ ምክንያት ስታሰር ከመንከራተት ስጣላ እንዳይሞትብኝ ብላ ከመስጋትና በየፀሎት ጓዱ ስሜን እየሰጠች አልቅሳ ከመፀለይ ውጪ ክፉ ተናግራኝ አታውቅም የኔ እናት በቄ። "አቤልዬ ና እስኪ" ስትለኝ "አቤት ምንድነው" ብዬ የነበረችበት ኩሽና ከፊቷ በነበረች ዱካ ላይ ቁጭ አልኩኝ። አጠገቧ ቁጭ ካልኩ ላደርገው ምችለው ነገር ብር ፈልጫት መውጣን እንደሆነ እሷም እኔም እናውቃለን። "ህልም አይቼ ልነግርህ ነው" አለችኝ ፈራ ተባ እያለች። ምላሴ ረጅም ስለሆነ ምናገራት ነገር ይሰቃታል። "እሺ ቶሎ በይ ቀን ምታስቡትን ማታ እያያቹ ታሰቃዩናላቹ" አልኳት ስትጨርስ ብር ፈልጫት ለመሄድ እያሰብኩ። "ቁጭ ብዬ ስላንተ እያሰብኩ ባለበት ፊቱ ከብርሃን የሚያበራ ለማየት የማይሞከር ድምፁ የሚያስፈራ እረዘም ያለ ሰው ወደኔ መጥቶ…" ስትል ውስጤ "ኢየሱስ" የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶኝ መስማቴን ቀጠልኩ። "…ልጄ ሆይ አትፍሪ ልጄ በእናተ ጭቅጭቅ ሳይሆን በእኔው መንገድና ጊዜ ነው የሚመለሰው አትጨቅጭቁት ብሎ ከአጠገቤ ተሰውረ" ብላኝ በረጅሙ ተነፈሰች። የነገረችኝ ህልም ቀን ስታስቢው የዋልሽውን ነው ያየሽው ብዬ አቅልዬ እንደማላልፈው ውስጤ ቢያውቅም እሷ ፊት የግርምት ፊት ላለማሳየት ተጠንቅቄ የተቀመጥኩበትን ብር ተቀብዬ ወደ መንገዴ ፊቴን አዞርኩኝ። መንገድ ስሄድ እናቴ የነገረችኝ ህልም እያሰላሰልኩ ነበር፤ ሰሞኑን ቤት ውስጥ ከትንሹ ወንድሜ ጀምሮ ታላቅ እህቴ እናቴን ጨምሮ ምን ይሻልሃል እንዲ ሆነ ትቅር በሚል ምክራቸውና ወቀሳቸው ከመማሬ ጋር ተገጣጥሞብኛል። "ብለህ ብለህ ከመንገድህ እርቄ ጠፍቼ ላለሁት ለኔ ልጄን አትጨቅጭቁት ብለህ ትሟገትልኝ ጀመርክ" እያልኩኝ ዕንባ በጉንጬ ላይ እየፈሰሰኝ ነበር "በቃ ተወኝ በምህረትህ አታሰቃየኝ አጥፍቻለው፤ ሲልህ ቅጣኝ ሲልህ ጋህነብ አስገባኝ ዝም ብዬ ስበድልህ በምህረትህ አትቅጣኝ" አልኩ ለራሴ። እኔ በውስጤ ማወራ ይምሰለኝ እንጂ በአጠገቤ የሚያልፉ ሰዎች እንደ እብድ አወራ እንደነበር አስተያየታቸው ዘግይቶ ነበር የገባኝ።